የስኳር አቅርቦት እየተስተካከለ ነው

sugar largeባለፈው ዓመት የተከሰተው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በስኳር ምርት ላይ ባደረሰው ከፍተኛ ተጽዕኖ ምክንያት ከመስከረም 2010 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ያጋጠመ ጊዜያዊ የስኳር አቅርቦት ችግር እየተስተካከለ ነው፡፡

ችግሩን ለመፍታት ስኳር ኮርፖሬሽን ከአልጄሪያና ታይላንድ የገዛው 700 ሺ ኩንታል ስኳር ከጥቅምት 12/2010 ዓም ጀምሮ ከጅቡቲ ወደብ እየተጓጓዘ በመተሓራና ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች እንዲሁም በአዳማና አዲስ አበባ በሚገኙ መጋዘኖች እየተራገፈ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የስኳር አቅርቦትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በተያዘው በጀት ዓመት 7 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ስኳር እንደሚያመርቱ ከሚጠበቁ ስምንት ፋብሪካዎች ውስጥ የተንዳሆና የከሰም ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ የተቀሩት ፋብሪካዎችም ከህዳር ወር መጀመሪያ አንስቶ በተቀመጠላቸው የምርት ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡

ከውጭ የገባው ስኳር ከሰኞ ጥቅምት 20/2010 ጀምሮ ለአዲስ አበባ ሸማቾች፣ ለክልሎችና ለኢንዱስትሪዎች እንደየኮታቸው መጠን እየተከፋፈለ ነው፡፡

ዘንድሮ ከስኳር ፋብሪካዎች በሚገኘው ምርት የሀገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን በራስ አቅም ለማሟላት ታቅዶ መጠነ ሰፊ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

Top