ከውጭ ሀገራት የተገዛው ስኳር ወደተለያዩ መጋዘኖች እየተጓጓዘ መሆኑ ተገለጸ

Sugar We21የስኳር እጥረቱን ለመፍታት ከውጭ አገራት ከተገዛው 700 ሺህ ኩንታል ስኳር ግማሹን ወደተለያዩ መጋዘኖች እያጓጓዘ መሆኑን የስኳር ኮርፖሬሽን ገለጸ።

 ባለፈው ዓመት በተከሰተው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ምክንያት ከመስከረም 2010 ጀምሮ በመላ አገሪቱ የስኳር እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ይታወቃል።

 ችግሩን ለመቅረፍም  ከአልጀሪያና ታይላንድ 700 ሺህ ኩንታል ስኳር እንደተገዛ ተገልጿል።

 በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከተጠቀሰው መጠን ውስጥ ከ327 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ከጅቡቲ ወደብ ወደ ማከፋፈያዎች በመጓጓዝ ላይ ነው።

እስካሁን ባለው ሂደት በመተሃራና ወንጂ ስኳር ፋብሪካዎች እንዲሁም በአዲስ አበባና አዳማ መጋዘኖች 200 ሺህ ኩንታል ስኳር መራገፉን ተናግረዋል።

የመተሃራና ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች ለክልል ህብረት ስራ ማህበራት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት (ጅንአድ) እና አለ በጅምላ፤ የአዲስ አበባ መጋዘኖች  ደግሞ ለአዲስ አበባ ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም የአዳማ መጋዘኖች ለኢንዱስትሪዎች ስኳሩን ያከፋፍላሉ።

አዲስ አበባ ባሉ ሶስት የጅንአድ ማከፋፈያዎች ለህብረተሰቡ ይከፋፈል የነበረውን 112 ሺህ ኩንታል ስኳር ወደ 120 ሺህ ኩንታል ከፍ እንዲል መደረጉንም ጨምረው አብራርተዋል።

በቀጣይ አቅርቦቱን በዘላቂነት ለመፍታት በያዝነው ዓመት ከስምንት ፋብሪካዎች ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለማምረት አቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

የተንዳሆና ከሰም ስኳር ፋብሪካዎች ማምረት መጀመራቸውን የገለጹት አቶ ጋሻው "ቀሪዎቹ ከህዳር ወር ጀምሮ ወደ ስራ ይገባሉ" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በበኩሉ በከተማዋ ባሉ ሶስት የጅንአድ ማከፋፈያዎች የስኳር ምርቶች እየተከፋፈሉ መሆኑን ገልጿል።

የቢሮው ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ወልደሰንበት እንዳሉት፣ እስከ ትናንት ድረስ ከጅንአድ ቁጥር 6 መጋዘን ብቻ 21  የከተማዋ ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ስኳር የወሰዱ ሲሆን በቀሪዎቹ ሁለት የጅንአድ መጋዘኖች ላይም ምርቱ እየተከፋፈለ መሆኑን አክለዋል።

 አቶ በላይነህ እስካሁን ሙሉ ድርሻቸውን ያልወሰዱ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት የትራንስፖርት ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ገልጸው፤ ተሽከርካሪዎችን በመከራየት ድርሻቸውን ቶሎ መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

 በየደረጃው ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አመራሮች የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው ቸርቻሪ ነጋዴዎች ምርቱን ለህብረተሰቡ እንዲያደርሱ  ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ምንጭ፡- ኢዜአ ጥቅምት 22/2010ዓ.ም

Top