የከሰም ስኳር ፋብሪካ ለሸንኮራ አገዳ አብቃይና አቅራቢ አርብቶ አደሮች ከ9.6 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ፈጸመ

k2የከሰም ስኳር ፋብሪካ በሸንኮራ አገዳ አብቃይነትና አቅራቢነት ለተደራጁና ወደ ሥራ ለገቡ የአዋሽ ፈንቲአሌ ወረዳ አርብቶ አደሮች በ2008 ዓ.ም ለፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ አቅርበው ያገኙትን ከ9.6 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ፈጸመ፡፡ በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የሀርጌቲ ደነባ የሸንኮራ አገዳ አብቃይ ገበሬዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ ኅብረት ሥራ ማህበር ከስድስት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ያስገነባውን ዘመናዊ ሕንፃ አስመርቋል፡፡

ለከሰም ስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ አልምተው ለማቅረብ የተደራጁ ማህበራት 11 ሲሆኑ፣ ፋብሪካው ክፍያ የፈጸመው ወደ ሥራ ለገቡትና 397 አባላትን ላቀፉት ሚራህቶ፣ ቦንቲ ጎና፣ ከዳ ደሆ፣ አዳ ጉርቶ እና ሀመዳስን ለተሰኙ ማህበራት መሆኑን የፋብሪካው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የላከልን ዘገባ ያመለክታል፡፡ 

ለአርብቶ አደሮቹ የትርፍ ክፍያው በተፈጸመበት ወቅት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተገኑ ገናሞ ባደረጉት ንግግር በአገዳ አልሚነትና አቅራቢነት የተደራጁ የአካባቢው አርብቶ አደሮች ተግተው በመስራታቸው ለውጤት መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም በሸንኮራ አገዳ አልሚነትና አቅራቢነት የተደራጁ የመሰል ማህበራት አባላት የአምስቱን ማህበራት ፈለግ ተከትለው ከሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡፡

ተጠቃሚ የሆኑ አርብቶ አደሮች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ፋብሪካው የአካባቢውን አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ስትራቴጂ ቀይሶ ተግባራዊ በማድረጉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ከአሁኑ የተሻለ ገቢ ለማግኘት በከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚሰሩ አክለው ተናገረዋል፡፡

የከሰም ስኳር ፋብሪካ ለአርብቶ አደሮቹ በመስኖ የለማ መሬትና ምርጥ ዘር በማቅረብ እንዲሁም ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ በመስጠት ሸንኮራ አገዳ አልምተው ለፋብሪካው በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡          

በተያያዘ ዜና በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የሀርጌቲ ደነባ የሸንኮራ አገዳ አብቃይ ገበሬዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ ኅብረት ሥራ ማህበር ከስድስት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን ዘመናዊ ሕንፃ ግንቦት 12 ቀን 2009 ዓ.ም አስመርቋል፡፡

ሕንጻው ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች፣ ደረጃውን የጠበቀ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የዕቃ ግምጃ ቤት ዕና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡

በፋብሪካው ከተደራጁት ሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማህበራት መካከል አንዱ የሆነው የሀርጌቲ ደነባ የሸንኮራ አገዳ አብቃይ ገበሬዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ ኅብረት ሥራ ማህበር በ800 ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ አምርቶ ለወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የሚሸጥ ሲሆን፣ ከዚሁ የሚያገኙት ገቢም በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የፋብሪካው ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ዘገባ አመልክቷል፡፡

በሕንጻው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በማኀበር አባልነታቸው ከፍተኛ የሥራ አፈፃፀም ላሳዩ አባላት፣ ለግንባታው የሚሆነውን መሬት ለሰጡ ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎችና የተለያየ ድጋፍ ላደረጉ መስሪያ ቤቶችና ግለሰቦች የዋንጫ፣ የሠርተፊኬትና ሌሎች ሽልማቶች መበርከቱን የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡

Top