የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ

Tendaho Sugar Factoryjpgየአገሪቷን የስኳር ምርት ፍላጎት ለማሟላትና ምርቱን ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ  ምንዛሬ  ለማግኘት የጎላ ድርሻ የሚኖረው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በሚኒስትሮች /ቤት ደንብ ቁጥር 122/1998 ተቋቋመ፡፡ መንግሥት የተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክትን ከመጀመሩ አስቀድሞ   አዋጪነቱንና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ  ጠቀሜታዎቹን በበቂ ሁኔታ አጥንቶ ነው ወደ ስራ የገባው፡፡  ለዚህ  ግዙፍና ዘመናዊ  ፋብሪካ  እውን  መሆንም ታላቁ መሪ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ከሃሳብ ማመንጨት እስከ ፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ድረስ የነበራቸው ድርሻ የላቀ ነው፡፡

በአፋር ብሔራዊ ክልል 50ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳን በግብዓትነት የሚጠቀመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 660 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ግንባታው በሁለት ምዕራፍ የሚከናወነው ይህ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን 26ሺህ ቶን አገዳ ይፈጫል፡፡ የምርት መጠኑም ደረጃ በደረጃ እያደገ በአመት 619 ሺህ ቶን ስኳር እንደሚያመርት ይጠበቃል፡፡ ይህም ማለት አገሪቷ ያሏት ሦስት ነባር ስኳር ፋብሪካዎች በአመት በአማካይ የሚያመርቱትን የስኳር ምርት መጠን/300ሺህ ቶን/ ተንዳሆ ብቻውን ከእጥፍ  በላይ  ያመርታል  ማለት  ነው፡፡ 

በተጨማሪም ከስኳር ተረፈ ምርት ከሚያመነጨው 120 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ውስጥ 90 ሜጋ ዋቱን ወደ ናሽናል ግሪድ የሚያስገባ ሲሆን፣ 63 ሺህ ኪዩቢክ ኤታኖልም ያመርታል ተብሎ  ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ የአፋር አርብቶ አደር በመስኖ የሚለማ የእርሻና ግጦሽ መሬት እንዲያገኝ በማስቻል ለእንስሶቹ ሳርና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሲንከራተት ያሳለፈውን የጉስቁልና ሕይወት ከማሻሻል አንፃር የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

በግዙፍነቱ ብቻ ሳይሆን በተሻለ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነቱም ከሌሎቹ ነባር ስኳር  ፋብሪካዎች የሚለየው ተንዳሆ በየጊዜው ይፈጠሩ በነበሩ በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ምክንያት ሥራው ተጓቶ ቆይቷል፡፡ ይሁንና የስኳር ኮርፖሬሽን ከተቋቋመበት ጥቅምት 2003 . ወዲህ  ግን  ኮርፖሬሽኑ  በተከታታይ  በወሰዳቸው  እርምጃዎችና  ባደረጋቸው ማስተካከያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነበረበት ችግር ተላቆ በአሁኑ ወቅት የፋብሪካው የመጀመሪያ  ምዕራፍ  ግንባታ  ወደሚጠናቀቅበት  ደረጃ  ላይ  ሊደርስ  ችሏል፡፡ ወደዚህ የስኬት ምዕራፍ የተደረሰውም የአፋር ክልል መንግሥትን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመቀናጀት በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ዙሪያ የቅርብ ክትትልና ግምገማ ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡

ለፋብሪካው  ከሚያስፈልገው  50ሺህ  ሄክታር  መሬት  ላይ  የሚለማ   ሸንኮራ  አገዳ   ውስጥ   25ሺህ   ሄክታሩ  የሚለማው   በአውትግሮውርስ  ሲሆን፣  በመጀመሪያ ምዕራፍ እየተገነባ  ለሚገኘው ፋብሪካ  ከሚያስፈልገው 25 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 10ሺህ 572 ሄክታሩ  በተንዳሆ  ስኳር  ልማት  ፕሮጀክት  በአገዳ  ተሸፍኗል፡፡ የፋብሪካው የመጀመሪያ ምዕራፍ 2006 በጀት ዓመት አጋማሽ ተጠናቆና ሙሉ ፋብሪካው ተፈትሾ  ወደ ስኳር ማምረት ይሸጋገራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሁለተኛው ምዕራፍ ስራም የመጀመሪያው  አገልግሎት መስጠት በጀመረ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ታሳቢ ተደርጓል፡፡

የፋብሪካው የአገዳ ልማት የሚከናወነው በአዋሽ ወንዝ ላይ በተገነባው የተንዳሆ ግድብ አማካኝነት ነው፡፡ 1.86 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በላይ የመያዝ አቅም ያለው ይህ ግድብ 60 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማልማት ይችላል፡፡ ከተንዳሆ ግድብ ተነስቶ አገዳው በሙሉ እስከሚለማበት አሳኢታ ድረስ ካለው 67 ኪሎ ሜትር የዋና ውሃ መውሰጃ ቦይ (Main Canal) ውስጥ 44 ኪሎ ሜትሩ ተጠናቆ የመስኖ ልማት ላይ ውሏል፡፡

ከእነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን የስኳር ልማቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችን የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በተሟላላቸው መንደሮች በማሰባሰብ ቋሚ ኑሮ እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው፡፡ በዱብቲ በሦስት መንደሮች (አስቦዳ፣ አንድለቡሪና ቦይና) 1,500 አባወራ/እማወራ በመንደር ተሰባስበዋል፡፡

የአካባቢው አርብቶ አደሮች ከእንስሳት እርባታ በተጨማሪ በእርሻ ሥራ እንዲሰማሩ ለማስቻል መስኖ ገብ መሬት አዘጋጅቶ ከመስጠት እስከ ሁለንተናዊ የባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ድረስ የዘለቁ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት /ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ መስጊድ፣ ወፍጮ ቤት እና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከመንደር ማሰባሰብ ስራ ጋር አብረው በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የሰባት ማህበራዊ ተቋማት ግንባታዎች በሰባት መንደሮች (ቦይና፣ አስቦዳ፣ ኢቲሉ፣ እንደቡሪ፣ ጋሱሪ፣ አንደለቡሪና ዋይዴዴኤስ) ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለክልሉ ርክክብ ተፈጽሟል፡፡ በሁለት መንደሮች (ሄድለቡሪና ኪፊሉ) ደግሞ ግንባታቸው በአማካኝ 77.5% ደርሷል፡፡ በሌላ በኩል በዱብቲ ጋብላይቱ፣ በአይሮላፍ፣ ጋሱሪና ኡንዳቡሪ እየተሰሩ ካሉ የመስኖ መሬት ዝግጅቶች ውስጥ የተጠናቀቀውን 2,119 / 1,577 አባወራ/እማወራ በማከፋፈል ማልማት ተጀምሯል፡፡ 7,910 / የመስኖ እርሻ መሬት ደግሞ በዝግጅት ሂደት ላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ ለክልሉ ተወላጆች ወደ 12 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ በመስኖ የሚለማ የእርሻና የግጦሽ መሬት ለማስረከብ እየሰራ ነው፡፡

በፕሮጀክቱ የተፈጠረ የሥራ እድልን በተመለከተ እስካሁን 7ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ፣ ቋሚና የኮንትራት የስራ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ከኮንትራትና ቋሚ ሠራተኞች ውስጥ 430 በላይ የሚሆኑት በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑና እስከ ኃላፊነት ደረጃ የደረሱ የአፋር ብሔረሰብ ተወላጆችና የአካባቢው ማህረሰብ ሲሆኑ፣ ካሉት አጠቃላይ ሰራተኞች 37 በመቶውን ድርሻ ይዘዋል፡፡

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር 50 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር እና በዚህ ጊዜም የአካባቢው ተወላጆች እና ነዋሪዎች ከአሁኑ  በተሻለ ሰፊ የስራ ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከአፋር ክልል ጋር በመተባበር ለክልሉ ተወላጆችና ነዋሪዎች በእርሻ ስራና በቴክኒክ ሙያዎች ላይ ስልጠናዎችን በመስጠት ሄድ ማኖች፣ ፎርማኖችና የማሽን ኦፕሬተሮች ሆነው በፕሮጀክቱ እንዲቀጠሩ እያደረገ ነው፡፡

ከሚያስገኘው በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች አንጻር ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ግዙፉ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የአገሪቷን የስኳር ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ለስኳር ልማት ዘርፍ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

Top