የኦሞ ኩራዝ ፍሬ

omoከስኳር ጋር የሚተዋወቅ አብዛኛው ህዝብ ስኳር በማንኪያ ሲሰፈር እንጂ “በመጥረቢያ ሲፈለጥ” ሊያይ አይችልም አሁን፡፡ ይህ ደግሞ ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተያይዞ የዘመናችን ስኳር በብዛት የሚመረተው በቅንጣት መልክ በመሆኑ ነው፡፡ ጣፋጩ ስኳር ከሕንድ ወጥቶ እንዲህ እንደ አሁኑ ዓለምን ከማዳረሱ በፊት እንደ አሞሌ ጨው ሁሉ ጠፍጣፋ ሆኖ ይመረት እንደነበር መረጃዎች          ይጠቁማሉ፡፡ እናም ሻይ ቡናን ለማጣፈጥ ማንኪያ ከመጠቀማችን በፊት “የስኳር መጥረቢያ” መጠቀም የግድ የነበረበት ዘመን ታልፏል፡፡ እንዲህ እንደ አሁኑ በየሰፈር ሱቅ ከመገኘቱ በፊት ሃብታም በሚባሉ እና በነገሥታቱ እልፍኝ ብቻ የሚገኝና ምድቡ ከውድ ቅመማ ቅመም ተርታ የሚመደብ ወሳኝ ሸቀጥ ነበር ስኳር፡፡   እጅግ ውድ ስለነበረም ነጭ ወርቅ ተባለ፤ እንደ ወርቅም በቁጠባ ሒሳብ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡

በናፖሊዮን ጦርነቶች ወቅት ናፖሊዮን ወደ አውሮፓ በሚገቡ መርከቦች በተለይ ስኳር በጫኑት  ላይ ቁጥጥር በማጥበቁ የስኳር ዋጋ ሰማይ ነካ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር የአውሮፓ ሀገራት ከሹገርቢት (ስኳር ድንች የሚመስል ተክል) ስኳር ማምረት የጀመሩት፡፡ ቀስ በቀስም ስኳር ከበቆሎ እና ሌሎች እጽዋት መመረት ጀመረ ፡፡

የስኳር ቴክኖሎጂ እየተሻሻለ ሲመጣም ዋጋው እያደር በመቀነሱ በሁሉም ዘንድ ተፈላጊነቱ ሊጨምር ቻለ፡፡ በዛው መጠን የፋብሪካዎች ብዛት እና የምርት ጥራትም እያደገ መጣ፡፡ ይሁን እንጂ የህዝብ ቁጥር እጅግ በመጨመሩ ስኳርን በግብዓትነት ለሚጠቀሙ ኢንደስትሪዎች እና ለሰዎች ፍላጎት የሚሆን በቂ ስኳር ማቅረቡ ላይ አልፎ አልፎ እጥረቶች መከሰታቸው አልቀረም፡፡

ወደ ሀገራችን መለስ ስንል የስኳር ኢንደስትሪ ታሪክ ከ60 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡       ኢንደስትሪው “ሀ” ብሎ ሲጀምር ምርቱን ለማስተዋወቅ ስኳር በነጻ እስከ መስጠት መደረሱ አይዘነጋም፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር እነ ምኒሊክ ወስናቸው “ስኳር ስኳር … ነሽ ጣፋጭ” ብለው  ያቀነቀኑት፡፡

በወቅቱ ህዝቡ ቀስ በቀስ ምርቱን እየለመደው መጣ፤ ይሁንና የፋብሪካዎች (ወንጂ ሸዋ፣ መተሓራና ፊንጫአ) ቁጥር ባለበት በመቆሙ ስኳርን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንደስትሪዎች ብሎም የፈላጊው ህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅጉን ተመነደገ፡፡ ይህ በመሆኑም የስኳር ፍላጎትን ለማርካት ተጨማሪ የስኳር ፋብሪካዎችን መገንባት በተለይ ምጣኔ ሀብቷ በፍጥነትና በተከታታይ እያደገ ለመጣው ኢትዮጵያ የግድ ብሏታል፡፡

ከዚህ አኳያ የኢፌዴሪ መንግሥት በተለያዩ የሀገሪቷ ቆላማ አካባቢዎች 10 አዳዲስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችን እየገነባ ሲሆን፣ በማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካኝነትም ነባሮቹን ስኳር ፋብሪካዎችን (ወንጂ ሸዋና ፊንጫአ) የማስፋፋትና የማዘመን ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት አራት አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎችን (ተንዳሆ፣ አርጆ ዲዴሳ፣ ከሰምና ኦሞ ኩራዝ 2) ወደ ምርት በማስገባት የስኳር ፋብሪካዎችን ቁጥር ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ ችሏል፡፡

አሁን በስራ ላይ ያሉትን ጨምሮ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚጠናቀቁ ስድስት ፋብሪካዎች በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ አስቀድመው ሥራ ከጀመሩት ጋር ተዳምረው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ (2012 ዓ.ም.) ወደ 28 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ያመርታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሚመረተው ስኳርም የሀገሪቱን የስኳር ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ምርቱን ወደ ውጪ በመላክ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያን ስኳር ፋብሪካዎች ብዛት ከእጥፍ በላይ ካሳደጉት አንዱ በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት እየተገነቡ ከሚገኙት አራት ፋብሪካዎች ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. ስኳር ማምረት የጀመረው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአዲስ አበባ በ900 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የፋብሪካውን ግንባታ በታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ሲጎበኙ እጅግ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን ገልጸው ከሁለት ወር በኋላ እንደሚመለሱና ስኳር እንደሚያዩ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ እንዳሉትም አልቀረም በመጋቢት ወር ከሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ጋር ፋብሪካውን በድጋሚ በጎበኙበት ወቅት ስኳር እያመረተ አግኝተውታል፡፡

በእርግጥ አሁን ላይ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት አልጀመረም፡፡ ገና በሙከራ ምርት ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ አንድ ስኳር ፋብሪካን ለውጤት ለማብቃት ከሚጠይቀው ልፋት አንጻር የፋብሪካው ጅምር ጥሩ ነው፡፡ 

ስኳር ፋብሪካን ፋብሪካ ለማለት እንደ ሌላ ኢንዱስትሪ ማሽን መትከል ብቻ በቂ አይደለም፤ ምክንያቱም ከፋብሪካ ግንባታ ጎን ለጎን ትላልቅ ግድብ መገንባት፣ የመስኖ መሰረተ ልማት አውታሮች መዘርጋት፣ ሸንኮራ አገዳ ማልማት እንዲሁም በሺዎች ለሚቆጠሩ የፋብሪካው ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ቤቶች እና ሌሎች የማህበራዊና የመሰረተ ልማት ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋልና፡፡

ከዘርፉ ስፋትና ከሚጠይቀው መዋለ ነዋይ አንጻር የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ብዙ ውጣ ውረዶችና ተግዳሮቶች ይበዙበታል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በማለፍ በሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ 28 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ማምረት ላቀደች ሀገር የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ፍሬ ታላቅ የምስራች ነው ፡፡

ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ ሐምሌ 2006 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ አሁን ላይ 94 በመቶ ሥራው የተጠናቀቀው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ በዚህ ዓመት በቀን እስከ 6 ሺህ 500 ቶን ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ሥራ ውስጥ የገባ ሲሆን፣ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ግን በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ በመፍጨት 12 ሺህ ኩንታል ስኳር ማምረት ይችላል፡፡ በዓመትም 2.5 ሚሊየን ኩንታል ስኳር እና 28 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሚያመነጨው 60 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 20 ሜጋ ዋቱን ተጠቅሞ 40ውን ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ያስገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአጠቃላይ በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ ለሚገኙት የኦሞ ኩራዝ አንድ፣ሦስት እና አምስት፤ ለጣና በለስ 1 እና 2 እንዲሁም ለወልቃይት ስኳር ፋብሪካዎች ተስፋን ፈንጥቋል - የኦሞ ኩራዝ 2 ስኳር ፋብሪካ፡፡  

Top