ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የፈሰሰበት የስኳር ልማት ዘርፍ አሁንም ፍሬ እየሰጠ ነው

የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነድፎ ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ አንድም ጊዜ እንኳ ሀገራችን እጅግ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በሚፈልግና በርካታ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በሚካሄዱበት ልማት ላይ ተሰማርታ አታውቅም።

ሀገሪቷ ከስኳር ኢንዱስትሪ ጋር የተዋወቀችው 60 ዓመታት በፊት ኤች.. ከተባለ የኔዘርላንድስ ኩባንያ ጋር በአክሲዮን መልክ በዘርፉ በተሰማራችበት ወቅት ነው። በዚያን ወቅትና ከዚያም በኋላም በነበሩት ዓመታት በሀገሪቱ ነባር የተባሉት የስኳር ፋብሪካዎች ይገነቡ የነበሩት አንድን የስኳር ፋብሪካ በአንድ ወቅት ብቻ የመገንባት አካሄድን በመከተልና በውጭ አገር ኩባንያዎች ብቻ ነበር።

ከዚህ የሀገራችን የስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ታሪክ በተለየ መልኩ በስኳር ኢንዱስትሪ ልማት ረገድ ወገብ የሚያጎብጥና 10 አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎችን በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመገንባት ዕቅድ ተነድፎ ወደ ትግበራ የተገባው በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ነበር።  እነዚህ 10 ፋብሪካዎች ግንባታቸው የተጀመረው ለልማቱ በተመረጡ የተለያዩ ክልሎች ቆላማ አካባቢዎች ሲሆን፣ ቦታዎቹም በወቅቱ ከምንም ዓይነት መሰረተ ልማት አውታር ጋር የማይተዋወቁበት ሁኔታ ነበር። በዚህ ዘመናዊና ውስብስብ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ግንባታ ላይ በሀገር ደረጃ የካበተ ልምድ ያልነበረ ከመሆኑ ባሻገር ወደ ግንባታው ከመገባቱ አስቀድሞም በርካታ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት በጣም ሰፊ ጊዜን ይጠይቅ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከተነደፉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል እንደ ስኳር ልማት ዘርፍ እጅግ ከባድና ፈታኝ ፕሮጀክት አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።

ሌላውና ዘርፉን ከሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል እጅግ ግዙፍ የሚያደርገው ምክንያት የከፍተኛ ግድብ፣ ውኃ መቀልበሻ /ዊር/ ረጅም ርቀትን የሚሸፍኑ የዋና፣መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ አውታር ግንባታዎችን፤እጅግ ሰፊ የሆነ የእርሻ መሬትን ለአገዳ እርሻ ከማስተካከል በተጨማሪ በዚህ ሰፊ መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ የመትከል ስራን እንዲሁም ዘርፉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያሳትፍ እንደመሆኑ መጠን በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያና መኖሪያ ያልሆኑ ቤቶችን መገንባትን፤ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የተለያየ ደረጃ ያላቸውን /ቤቶች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ  አውታሮችንና ሌሎች በርካታ ግንባታዎችን ማከናወንን የሚጠይቅ በመሆኑም ጭምር ነው። ለዚህም ነው  “አንድ ስኳር ፋብሪካን መገንባት አንድ ከተማን መመስረት እንደ ማለት ነውየሚባለው።

የስኳር ፋብሪካዎችን ለረጅም ዓመታት በመምራት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ የዘርፉ ባለሙያዎችምየስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ መሆን የከተማ ከንቲባ እንደ መሆን ነውሲሉ ይደመጣሉ። ለዚህ አባባል ምክንያት የሚሆነውም የአንድ ስኳር ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ የፋብሪካውን የዕለት ከዕለት የፋብሪካ ኦፕሬሽን እና እጅግ ሰፊ በሆነ የአገዳ እርሻ መሬት ላይ የሚከናወን የአገዳ ልማትን ከመምራት በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ የፋብሪካው ሰራተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን የዕለት ከእለት ፍላጎት ማለትም የንጹህ መጠጥ ውኃ፣የኤሌክትሪክ ኃይል፣የጸጥታ ሁኔታን እንዲሁም የገበያ፣የትራንስፖርት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የአካባቢ ንጽህና፣የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና ሌሎች አንድ ማኅበረሰብ እንደ መሰረታዊ ፍላጎቶችና እንደ ምቾት ማግኛ አድርጎ ዘወትር የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች መሟላታቸውንም የሚከታተል በመሆኑ ነው።

2f2f3

ይህን ግዙፍ ኤክስፖርት-መር የስኳር ኢንዱስትሪ 2003. ጀምሮ እየመራ የሚገኘው የስኳር ኮርፖሬሽን ከሀገር በቀልና የውጭ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ልማቱን ከዳር ለማድረስ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ለቀጣይ ስኬት መደላድሎችን ፈጥሯል፡፡ በዚህም አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል። በተለይም ምንም ዓይነት የመሰረተ ልማትና የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ባልነበሩባቸው አካባቢዎች ተቋማቱን መገንባቱ እንደ አንድ ዓብይ  ስኬት የሚታይ ነው።

ሌላው ስኬት ደግሞ ምንም እንኳ የሀገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትና አቅርቦትን ክፍተት ለጊዜው ማጥበብ ባይቻልም በመጀመሪያው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የከሰም፣የአርጆ ዲዴሳ እና የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎችን ግንባታ አጠናቆ የሙከራ ምርት ማስጀመር ተችሏል። ይህም ላለፉት 20 እስከ 60 ለሚሆኑ ዓመታት ከምናውቃቸው ከወንጂ ሸዋ፣ ከመተሐራና ከፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካዎች የስኳር ምርቶች በተጨማሪ ከሌሎች ሶስት አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ምርቶች ጋር ያስተዋወቀንና አንድ እርምጃ ወደፊት መጓዛችንን የሚያመላክት ስኬት ነው።

በሌላ በኩል የፊንጫኣ እና የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅና በተሻለ አቅም ወደ ምርት መግባታቸው እንዲሁም በተለይ የቀድሞው የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በአዲስና ዘመናዊ ፋብሪካ መተካት የቻለው በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዓመታት ውስጥ ነው። የእነዚህ ሁለቱ ፋብሪካዎችና ሶስቱ አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች አጠቃላይ በቀን አገዳ የመፍጨት አቅማቸው 36ሺህ250 ቶን ይደርሳል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከመመስረቱ በፊት ሶስቱ ነባር የስኳር ፋብሪካዎች  የነበራቸው አገዳ የመፍጨት አቅም በቀን 13ሺህ900 ቶን ብቻ ነበር።

በተመሳሳይ በቀን 24ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም የሚኖራቸው የኦሞ-ኩራዝ ቁጥር 1 እና 2 አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች 2009. ወደ ምርት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በቀን 84ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም የሚኖራቸው የጣና በለስ1 እና 2 የኦሞ ኩራዝ 3 እና 4 እንዲሁም የወልቃይት ስኳር ፋብሪካዎች እስከ 2012. ድረስ ባሉት ዓመታት ተጠናቀው ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል

የአገዳ ልማትን በተመለከተም በአሁኑ ወቅት 96ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በአገዳ የተሸፈነ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ ከስድስት ዓመታት በፊት 30ሺህ397 ሄክታር ብቻ ነበር።

የስኳር ፋብሪካዎች የሰራተኞች የመኖሪያና አገልግሎት መስጫ ቤቶች ግንባታም እየተካሄደ ሲሆን፣ እስካሁን 4,218 የመኖሪያና 107 መኖሪያ ያልሆኑ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 2,526 የመኖሪያና 67 መኖሪያ ያልሆኑ ቤቶች ግንባታ በመፋጠን ላይ ይገኛል።

እንደ ማንኛውም ታዳጊ ሀገር ኢትዮጵያም የስራ አጥ ዜጎች የመብዛት ችግር እንደሚፈታተናት ይታወቃል። እናም ሀገሪቷ ለስኳር ልማት ያላት ዕምቅ አቅምን ታሳቢ በማድረግ ልማቱ  ሲወጠን ዒላማ ከተደረጉ ግቦች መካከል አንደኛው ዘርፉ ሊፈጥር የሚችለው ሰፊ የስራ ዕድል ነው። በመሆኑም ባለፉት አምስት ዓመታት የስኳር ልማት ዘርፍ እጅግ ሰፊ የስራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በዚህም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በዘርፉ 350 ሺህ ዜጎች ቋሚ፣ጊዜያዊ እና ኮንትራት ቀጥተኛ የስራ እድል ለመፍጠር ተችሏል። ከዚህም ባሻገር በስኳር ልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የገቢ ምንጭ ማግኘትና ኑሯቸውን መምራት ችለዋል። እዚህ ላይ ታዲያ የስኳር ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ዕውቀትና ክህሎት ካላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ ጉልበት ሠራተኞች ድረስ የሚሰማራበት መሆኑን ልብ ይሏል። የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በከፊል

ሌላው ከስኳር ልማቱ መደበኛ ስራ ጎን ለጎን ልማቱ በሚካሄድባቸው ቆላማ አካባቢዎች በስኳር ኮርፖሬሽን እየተገነቡ የሚገኙ የመሰረተ ልማት አውታሮችና የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ ይህም የኮርፖሬሽኑን የስራ ኃላፊነት ግዙፍ ከሚያደርጉት ተግባራት መካከል አንዱ ነው። በዚህ መሠረት 286 የመሰረተ ልማት አውታሮችና ማኅበራዊ ተቋማት የተገነቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል /ቤቶች፣ የጤና  ተቋማት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ ወፍጮ ቤቶች፣ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የማኅበራት ሱቆች እንዲሁም የእንስሳት መጠጥ ውሃ እና ጤና ኬላዎች እና ሌሎች የማኅበራዊ ተቋማት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

በተጨማሪም በስኳር ልማት ፕሮጀክቶች አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች 524.5 ሄክታር በመስኖ የሚለማ መሬት በማመቻቸት የመረጡትን ሰብል እንዲያለሙ እየተደረገ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም በፕሮጀክቶችና ፋብሪካዎች አካባቢዎች የሚገኙ 11,817 አባወራ/እማወራዎች 75 የአገዳ አብቃይና አቅራቢ ማኅበራት ተደራጅተውና በመስኖ የሚለማ መሬት ተመቻችቶላቸው እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች አገዳ አልምተው ለፋብሪካው በማቅረብ ጥቅሙን መቋደስ ጀምረዋል። ከዚህ ባሻገር ኮርፖሬሽኑ የማኅበረሰቡን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ያከናወነው ተግባር ተገቢ ሆኖ በተገኘባቸው የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችና ፋብሪካዎች ለማኅበረሰቡ የካሳ ክፍያ በመፈጸም የመልሶ ማስፈር ስራ የማከናወን ተግባር ነው፡፡ ይህን ሲያከናውንም የመሰረተ ልማት አውታሮችና የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማሟላት ነው።

f7በሌላ በኩል 2007/08 . በኤልኒኖ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በመቀነስ ረገድ ኮርፖሬሽኑ ያስገነባቸው የግድብና የመስኖ መሰረተ ልማት አውታሮች የተጫወቱትን ሚና መጥቀስ ሌላው የስኳር ልማት ዘርፉ ፍሬ መገለጫ ነው። ከዚህ አኳያ የመተሐራ፣ ከሰምና ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎች እንዲሁም የጣና በለስና ወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በአካባቢያቸው ለሚኖሩና በድርቅ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከብቶቻቸው ውኃ እንዲሁም ለስኳር ምርት የማይፈለገውን የሸንኮራ አገዳ የላይኛው ጫፍ (ቶፕ ኬን) ሞላሰስና ሳር ለእንስሳት መኖ በማቅረብ ድርቁ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው የዘርፉ ፍሬ መስጠት መጀመር ሌላው ማሳያ ነው።  

በአጠቃላይ ማንም ሊገነዘበው የሚገባው ስኳር ኮርፖሬሽን ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲያከናውናቸው የቆዩት በርካታና ግዙፍ ተግባራት ያለ ከፍተኛ በጀት ከቶ ሊታሰቡ የሚችሉ አለመሆኑን ነው። ይህ ማለት ታዲያ ኮርፖሬሽኑ እነዚህን በርካታና ግዙፍ ተግባራትን በአንድ ጊዜ ሲያከናውን ምንም ዓይነት ጉድለት ሳይታይበት ነበር ለማለት አይደለም። ይልቁንም እነዚህን የመሳሰሉ ግዙፍና ውስብስብ ፕሮጀክቶችን ከመምራት አኳያ የሚያጋጥሙ የማስፈጸም አቅም ችግር፣ የሰለጠነ ባለሙያ እጥረትና የቴክኖሎጂ ክፍተቶች ስኳር ኮርፖሬሽንም የሚጋራ ነው የሚሆነው። በመሆኑም በስኳር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ረገድ፣ በፕሮጀክት እና በኮንትራት አስተዳደር የእውቀት ማነስ በኩል የታዩ ክፍተቶች እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ የባለሙያዎች ስራ መልቀቅ ረገድ የነበሩ ችግሮች በኮርፖሬሽኑ በኩል የታዩና ትምህርት የተቀሰመባቸው ጉዳዮች ናቸው።

ከላይ እንደተገለጸው በሀገራችን ነባር የስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ታሪክ ውስጥ ሀገር በቀል የሆነ ተቋም ሙሉ የግንባታ ተቋራጭ ሆኖ የተሳተፈበት ጊዜ አልነበረም። ዛሬ ላይ ግን ሀገር በቀል የሆነው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በሀገራችን የስኳር ኢንዱስትሪ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በፋብሪካ ግንባታ ላይ ተሰማርቶ የኦሞ ኩራዝ 1 እንዲሁም የጣና በለስ 1 እና 2 ስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም የሆነው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነድፎ ወደ ትግበራ በተገባበት ወቅት ነው።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሸን በሀገራችን የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ላይ ዋና ሥራ ተቋራጭ ሆኖ መሳተፉ በኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂ ተቀባይ  ብቻ ከመሆን አላቆ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማምጣትና ቴክኖሎጂን ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ታዲያ ይህ እንደ ሀገር አንድ ትልቅ እርምጃ ወደፊት ያስጓዘን ቢሆንም ግንባታቸው የተጀመረ የስኳር ፋብሪካዎችን በፍጥነት አጠናቆ ወደ ምርት ማስገባት ግን ቀሪው የቤት ስራ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ በሀገራችን የስኳር ፋብሪካ ግንባታ እየተሳተፉ የሚገኙ እና ከዚህ ቀደምም የተሳተፉ  የውጪ ሀገር ኮንትራክተሮች በኢንዱስትሪው 100 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱ መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል።

በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን በማሟላትና ተጨማሪ ስኳር አምርቶ ወደ ውጪ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መጀመር ሲገባን ምርቱን ከውጭ ለማስገባት እየወጣ ያለው የውጭ ምንዛሬ ያስቆጫል። ከዚህ በመነሳት ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና ሌሎች የሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ከእስካሁኑ ስኬታቸውም ሆነ ጉድለታቸው ትምህርት በመቅሰም በዘርፉ ሊደረስባቸው የታቀዱ ግቦች ስኬታማ ይሆኑ ዘንድ ይበልጥ ሊተጉ ይገባል። እነዚህ አካላት ብርቱ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ደግሞ የስኳር ልማት ዘርፍ ፍሬ እየሰጠ የመሆኑ ሐቅ ነው።

f8እዚህ ላይ ከሌሎች የዘርፉ ጥቅሞች በተጨማሪ ለአብነት ሊጠቀስ የሚችለው በቅርቡ ስኳር ኮርፖሬሽን የስኳር ተረፈ ምርት ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን ሞላሰስ ሮውኔት ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሀገር ውስጥ የግል ኩባንያ አማካኝነት ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ማስገኘት የጀመረው የውጭ ምንዛሬ ነው። ኮርፖሬሽኑ ከኩባንያው ጋር የካቲት 2008. ውል በመፈራረም ሀገራችን በዓመት 17 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ እንድታገኝ የሚያስችላትን ሞላሰስ ወደ እንግሊዝ ሀገር መላክ ጀምሯል፡፡ በቀጣይም በአመት እስከ 120 ሺህ ቶን ሞላሰስ ወደ ውጪ ለመላክ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የተላከውን ምርት የተረከበው ዩናይትድ ሞላሰስ ሊሚትድ ኦፍ ኢንግላንድ የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያም ምርቱን በመረከብ 80 በመቶ የሚሆነውን የዓለማችንን ሞላሰስ ወደሚያጣሩት የአውሮፓ ሀገራት ያከፋፍላል። ይህ የንግድ ግንኙነትም ምናልባት ወደፊት እነዚህን በሞላሰስ ማጣራት የተሰማሩ የአውሮፓ ኩባንያዎችን ወደ ሀገራችን በመሳብ የማጣሪያ ፋብሪካቸውን እዚህ እንዲተክሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። ለዚህም እንደ ዋንኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ከሌሎች ሞላሰስ አቅራቢ ከሆኑ የስኳር አምራች ሀገራት በተለየ ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ያላት ቅርበት ነው።

የተገነቡ ቤቶች  በአጠቃላይ በተጠናቀቀው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን  በዘርፉ እጅግ ቁጥሩ በርካታ የሆነ የሰው ኃይል በማሰለፍ የተከናወኑት መጠነ ሰፊ የልማት ሥራዎች መንግሥት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ባይመድብ ኖሮ የሚታሰቡ አልነበሩም። ከዚህ አንጻር የስኳር ልማት ዘርፍ በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ከተመደበላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ይህ በመሆኑም በዘርፉ የፈሰሰው ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በአይን በሚታዩ እጅግ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ላይ ውሎ የስኳር ልማቱ ፍሬውን እየሰጠ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተሻለ አፈጻጸም የዘርፉን ግቦች ለማሳካት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ስለሆነም ለዘርፉ ስኬት የመንግሥት ተገቢ ድጋፍና የቅርብ ክትትል በእጅጉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን፡፡ ይህ ሲሆን ፍሬውን እየሰጠ የሚገኘው የስኳር ልማት በቅርቡ በነጩ ወርቅ ይበልጡኑ ያብባል!   

Top