የስኳር ልማት የኤልኒኖ ተጽዕኖን የመቀነስ ሚና

omo1enባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት የተከሰተው ኤልኒኖ የአየር ለውጥ በበርካታ የዓለም ክፍሎች በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ላይ ተጽዕኖውን አሳርፏል፡፡ የአየር ለውጡ ከሚንጸባረቅባቸው መንገዶች አንዱ ተጽዕኖው ባረፈባቸው ክፍላተ ዓለማት  የሚገኙ ወንዞች የውሃ መጠን መቀነስ ነው፡፡ በዚህም ኤልኒኖ በተለይ በዝናብ ወራት ወቅት ብቻ የእርሻ ስራ የሚያከናውኑ ሀገራትን የምጣኔ ሀብት መጉዳቱ የሚጠበቅ ነው፡፡

በሌላም በኩል የተሟላ የመስኖ መሰረተ ልማት ያላቸው ታላላቅ ግድቦች መኖር የአካባቢው የውኃ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውል እንዳይፈስ ማድረግ የሚያስችል በመሆኑ በተለይ ምጣኔ ሀብታቸው በዝናብ ወቅት በሚከናወን የእርሻ ስራ ላይ ጥገኛ በሆኑ ሀገራት ላይ ኤልኒኖ እያስከተለ ያለውን ድርቅ ለመቋቋም ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡

በኤልኒኖ ምክንያት ድርቅ ከተጋረጠባቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ሀገሪቱ ሰፊ የውሃ ሀብቷን በጥቅም ላይ ለማዋል በርካታ ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉና የሚያደርጉ ትልልቅ ግድቦች እና የመስኖ መሰረተ ልማቶች ሥራ እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ለአብነትም ለኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በተገነባው ጊዜዊ ግድብ (ኮፈር ዳም) አማካኝነት በልማቱ አካባቢዎች የሚኖረው  የህብረተሰብ  ክፍል በመስኖ  በቆሎ እያመረተ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል፡፡

እንደ ደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለፃ፣ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የአካባቢው ህዝብ በድርቅ እንዳይጠቁ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡ በዚህም በወይጦ፣ በዞ እና ኦሞ በተዘረጉት የመስኖ መሰረተ ልማቶች  በመጠቀማቸው  አካባቢያቸው  ለድርቅ አለመጋለጡን ነው አስተዳዳሪው የጠቆሙት፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረውን የሰላማጎ አካባቢን የድርቅ ተጋላጭነት ሲያወሱም የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ወደ አካባቢው ከመጣ ወዲህ ለወረዳው ምንም ዓይነት የምግብ እርዳታ አቅርበው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡የውሃም ሆነ የከብቶች መኖ እጥረት ገጥሞናል የሚል ሪፖርት እስካሁን አልደረሰንምየሚሉት  አቶ አለማየሁ  ይህ እንዲሆን ያስቻለው የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ነው በማለት ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ያለውን ጠቀሜታ    አስረድተዋል፡፡

የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ የመስኖ መርሐ ግብር እርሻን የማያውቁ የቦዲ ብሔረሰብ ነባር እና አዳዲስ መንደሮች ነዋሪዎች በቆሎ በማምረት ለአራተኛ ጊዜ በሔክታር እስከ 70 ኩንታል ምርት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፤ ለአምስተኛ ጊዜም በቆሎ ለመዝራት በዝግጅት ላይ ናቸውየሚሉት ደግሞ በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት-1 የህዝብ አደረጃጀት፣ ካሳ እና መልሶ ማቋቋም ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አስረስ አደሮ ናቸው፡፡ 

የሰላማጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጳሺማ ወልኮሮ በበኩላቸው የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ወደ አካባቢው ከመግባቱ በፊት ወረዳቸው ለምግብ እጥረት እና እርዳታ የተጋለጠ መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን በኤልኒኖ ምክንያት በአካባቢው ምንም ዓይነት ተጽዕኖ እንዳልደረሰ ተናግረዋል፡፡

እንደሳቸው ገለፃ የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ በአካባቢው ከመከፈቱ በፊት ኦሞ ሻሺ በተባለ አካባቢ በአርብቶ አደሮች ይመረት የነበረ የበቆሎ ምርት መጠን እጅግ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ የአካባቢውን ዓመታዊ የምግብ ፍጆታ ለመሸፈን የማይታሰብ  ነበር፡፡  ከዚህ አንጻር የወረዳዋ ነዋሪዎች የምግብ  ዕርዳታ ይደረግላቸው እንደነበር እና  አሁን ግን ምንም አይነት እርዳታ እንደማይፈልጉ አረጋግጠዋል፡፡ በቀደሙ ጊዜያት ለራሳቸውና ለእንስሳታቸው ምግብ እና ውሃ ፍለጋ ይንከራተቱ የነበሩ አርብቶ አደሮችም አሁን በአቅራቢያቸው ማግኘት ችለዋል፡፡

omo3በፈቃደኝነት በመንደር ከተሰባሰቡት አርብቶ አደሮች አንዱ ናቸው የቦዲ ብሔረሰብ ተወላጅ አቶ ቦጪ ዶርባ፡፡ የመንደራቸው ሰዎች መጀመርያ አካባቢ ምን ያህል ፕሮጀክቱን ይጠራጠሩት እና እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ያዩት እንደነበር አስታውሰው፣ ኋላ ግን የቦዲና የሙርሲ ማህበረሰብ አባላት በመስኖ ልማት እየተጠቀሙ ያሉትን የደቡብ ኦሞ ዞን በና፣ ጸማይ፣ ዳሰነች እና ኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደሮችን ከጎበኙ በኋላ አመለካከታቸው መለወጡን ይናገራሉ፡፡

በሀገሪቱ ስኳር ልማትን በመጀመር ቀዳሚ የሆነውን ወንጂ ስኳር ፋብሪካንም ጎብኝተን ልምድ ተጋርተናል፡፡ ኢንደስትሪው ምን ያህል ተጠቃሚ አድርጎ የቀድሞ በምግብ እርዳታ ላይ የተንጠለጠለ ሕይወታቸውን እንደቀየረው ለመረዳት ችለናል፡፡ያሉት አቶ ቦጪ የዞን አስተዳደሩን እና የስኳር ልማት ፕሮጀክቱን መሬት ጠይቀው ለእያንዳንዳቸው 1 ሔክታር በመስኖ የሚለማ  የሸንኮራ አገዳ መሬት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ግባታው እየተፋጠነ የሚገኘው ፋብሪካ ቁጥር 1 ስኳር ማምረት የሚጀምርበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የሸንኮራ ማሳቸውን ከመንከባከብ ጎን ለጎን በፕሮጀክቱ እገዛ በቆሎ ለአራተኛ ጊዜ አምርተው ለአምስተኛ ዙር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ የውኃ ኩሬዎች በየመንደሩ ስለተዘጁላቸውም ውሃ እና የግጦሽ መሬት ፍለጋ ሩቅ መኳተኑ ቀርቶልናል ብለዋል፡፡  ልጆቻቸውም መንደራቸው ላይ በተገነባው ትምህርት ቤት እየተማሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ለመስኖ የሚጠቀመውን የኦሞ ወንዝ ውሃን መጠን አስመልክቶ የፕሮጀክቱ መስኖ ግንባታ እና ጥገና ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ጌታቸው እንደተናገሩት፣ ፕሮጀክቱ በዋና እና ተጨማሪ የመስኖ ቦዮች ከኦሞ ወንዝ ከሚወስደው 22.76 ሜትር ኪዩብ ውሃ ውስጥ 0.0023 ሜትር ኪዩብ ብቻ ተጠቅሞ የተቀረውን ወደ ወንዙ ይመልሳል፡፡

በተመሳሳይ ከጊቤ ኃይል ማመንጫ ለዚሁ ዓላማ የሚውለው ውሃ ተመልሶ የሚገባው ወደ መደበኛ መስመሩ ሲሆን፣ ይህም በወንዙ የውሃ መጠን ላይ ምንም መዋዠቅ ያለማስከተሉ ታውቋል፡፡

omo4enባለፉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ እያስፋፋች ያለችው ትላላቅ የመስኖ መሰረተ ልማት ሥራ በተለይም ከሸንኮራ ልማት ጋር ተያይዞ የሚካሄደው የመስኖ ልማት አውታር ኤልኒኖን ማስቀረት ባይችልም እንኳ ልማቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የድርቅ ጉዳት እንዳይከሰት ግን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ 

በአጠቃላይ በኤሊኒኖ ምክንያት በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የማኅበረሰብ አባላት ንጹህ የመጠጥ ውሃ፤  ለእንስሳት  ደግሞ ውሃ፣ ለስኳር ምርት የማይውለውን የሸንኮራ አገዳ የላይኛው ክፍል እና እስር ሣር በማቅረብ  ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የአፍሪካ የውሃ ማማ የምትባለው ኢትዮጵያ ሰፊ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ ለመጠቀም መብቱ እንዳላት ይታወቃል፡፡ ከዚህ የተነሳ የኢ... መንግሥት የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስና ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ የሀገሪቱን ውሃ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ትልልቅ እና አነስተኛ የመስኖ ግድቦች እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም በቀጣይ ኤልኒኖንም ሆነ ሌሎች መሰል ተጽእኖዎችን ለመቋቋም ያስችላል፡፡

Top