27ኛ ዓመት የግንቦት 20 የድል በዓል በስኳር ኮርፖሬሽን ተከበረ

Billboard banner2የግንቦት ሃያ 27ኛ ዓመት የድል በዓል “የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለላቀ አገራዊ ስኬት!” በሚል መሪ ቃል በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና መ/ቤት ግንቦት 17/2010 ዓ.ም ተከበረ፡፡

በዚህ ክብረ በዓል ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ወዮ ሮባ በኢህአዴግ መሪነትና በመላ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከፍተኛ ትግልና መስዋዕትነት የደርግ ሥርዓት ተገርስሶ አገሪቷ ወደ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ጎዳና ከተሸጋገረች 27 ዓመታት መቆጠሩን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በእነዚህ ዓመታት መላውን ሕዝብና ልማታዊ ባለሃብቶች ከጎኑ አሰልፎ የጸረ-ድህነት ትግሉን አጠናክሮ በማስቀጠል አገሪቷ ተከታታይና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ መቻሉን ገልጸው፣ ይህም ስኬት አገሪቷ የምትከተለው የፌደራል ሥርዓት ያስገኘው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በፌደራል ሥርዓቱ አማካይነት የመጣውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ለማረጋገጥ ከተወጠኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የስኳር ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ወዮ፣ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት በዘርፉ ባጋጠሙ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሳቢያ የታቀደውን ያህል ውጤት ማግኘት ባይቻልም እንኳ በተከናወኑ መጠነ ሰፊ ሥራዎች አገሪቱ በ2016 ዓ.ም የአለም የስኳር ገበያን መቀላቀል የምትችልበትን እድል እውን የሚያደርጉ መደላድሎችን ለመፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም በዘርፉ የተጀመሩ ሰፋፊ ሥራዎችን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ቀሪ ሁለት ዓመታት በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሠራተኞች የዘንድሮው የግንቦት 20 የድል በዓል ቃል የሚገቡበት ታሪካዊ ቀን ነው ያሉት አቶ ወዮ፣ ይህንን በመፈጸም የትግሉ ሰማዕታት ለሰላም፣ለልማትና ለዴሞክራሲ የከፈሉትን የሕይወት መስዋዕትነት ከዳር ማድረስ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የፌዴራሊዝም ብያኔ እና ምንነት፤ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር፤ የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት መገለጫዎች፣ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች እና የሚፈቱበት አግባብን ያካተተ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ በአቶ ፋሲል ገ/ማርያም የህግ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም በጽሁፍ አቅራቢውና በአወያዩ አቶ ገ/ዋህድ ዜናዊ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በዕለቱ ከደርግ ሥርዓት ጋር ሲፋለሙ የተሰዉ ሠማዕታትን ለመዘከር ሻማ የበራ ሲሆን የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎትም ተደርጓል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ከስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራሮች ጋር ትውውቅ አደረጉ

togaየመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራሮች ጋር ግንቦት 6/2010 ዓ.ም. በተቋሙ ተገኝተው ትውውቅ አደረጉ፡፡ በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ የሚገኝበትን ሁኔታ ጠቅለል ባለ መልኩ የሚያስቃኝ ፊልም እና የኢንዱስትሪውን አጀማመር፣ እድገት፣ ፈተናዎችና ተስፋዎች የሚገልጽ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ሚኒስትሩ በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአቶ እንዳወቅ አብቴ እና በሌሎች አመራሮች ከተደረገላቸው ገለጻ በኋላ በሰጡት አስተያየት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቀሪ ዓመታት በስኳር ልማት ዘርፍ የተጀመሩ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ለማሳካት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በተቋማዊ የአመራር ሥርዓት ግንባታ (Corporate Governance)፣ በአገር ውስጥ ፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ የውጭ ገበያና በጋራ የሚያለሙ (Joint venture) አጋሮችን በማፈላለግ እንዲሁም የክልል መንግሥታት የዘርፉን ልማት እንዲደግፉ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ በኩልም ከሁሉ በላይ የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸው የውስጡ ከተፈታ ውጫዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ይቻላል ብለዋል፡፡ ይህንን በመተግበር በመጪዎቹ ዓመታት ማምረት ያልጀመሩ አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ እንዲሁም ወደ ምርት ገብተው ነገር ግን በሙሉ አቅማቸው መስራት ያልጀመሩትን ደግሞ ሙሉ አቅማቸው ላይ እንዲደርሱ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የዚህን በጀት ዓመት አፈጻጸም በተቻለ መጠን ለማሻሻልም በቀሪዎቹ ሁለት ወራት እስካሁን የነበሩ ጥረቶችን እጥፍ ድርብ አድርጎ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

በዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ግልጽ የሆነና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ቅድሚያ ትኩረት ከሚሰጠው የኮርፖሬሽኑ ተልዕኮ ውስጥ ዋንኛው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ለአሠራር ምቹ በሚሆን መልክ የተቋሙን አደረጃጀት በመፈተሽና የሰው ኃይል ልማት ላይ ያለውን ክፍተት በመለየት በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት አቅምን መገንባት እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም የተቋሙን የምርምር ማዕከልና የስኳር አካዳሚን ከውጭ ሀገር ልምድ በመቅሰም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡ አክለውም ኮርፖሬሽኑ የጀመረውን የለውጥ ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠልና በአለም ተወዳዳሪ የስኳር ኢንዱስትሪ በመገንባት በሀገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነትን (Corporate Social Responsibility) በመወጣት በልማቱ አካባቢ የሚገኘው ማህበረሰብ “ልማቱ የእኔ ነው” ብሎ በባለቤትነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስና ልማቱን እንዲደግፍ ማድረግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ ግን ኮርፖሬሽኑ ሊያሳካ የተሰጠውን የቢዝነስ ተልዕኮ በሚያዛባ ደረጃ ሚዛኑን ስቶ መፈጸም እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል እሳቸው የሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ጨምሮ በዘርፉ ከተሰማሩ ሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር አገራዊ ተልዕኮን ለማሳካት ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ በማሳሰብ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በትውውቅ መድረኩ ላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በየነ ገ/መስቀልን ጨምሮ ሌሎች የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር ተገኝተዋል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ማምረት ጀመረ

ku2ከሙከራ ምርት በኋላ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት ለረዥም ወራት ስኳር ማምረት አቁሞ የነበረው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ከትላንት ታህሳስ 22 ቀን 2010. ጀምሮ ስኳር በማምረት መደበኛ ሥራውን ጀመረ፡፡

ስኳር ከማምረቱ ከሁለት ቀናት በፊት አገዳ በመፍጨት ሥራ የጀመረው ይህ ፋብሪካ ከሰኔ አጋማሽ 2009 . ጀምሮ ስኳር እንዲያመርት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በዝናብ ምክንያት ላለፉት ስድስት ወራት ወደ ሥራ ሳይገባ ቆይቷል፡፡ የአየር ንብረት መዛባትን ተከትሎ ባለፈው ዓመት በአካባቢው ባልተለመደ ሁኔታ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ሳቢያ በወቅቱ ለፋብሪካው ግብዓት የሚውል ሸንኮራ አገዳ ከማሳ በማውጣት ወደ ፋብሪካ መውሰድ አዳጋች ነበር፡፡

ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ በዓመት እስከ 2.5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳርና 28 ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ኤታኖል እንደሚያመርት ይጠበቃል፡፡

ለፋብሪካው ግንባታ ብቻ ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ 6.67 ቢሊዮን ብር ብድር ሐምሌ 2007 . ሥራው በይፋ የተጀመረው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ባጋስ ከተባለ የስኳር ተረፈ ምርት ከሚያመነጨው 60 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ውስጥ 20ውን ለራሱ ተጠቅሞ 40 ሜጋ ዋቱን ወደ ብሔራዊ ቋት የመላክ አቅም አለው፡፡

በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት እየተገነቡ ከሚገኙ አራት የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ የኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ አንዱ ሲሆን፣ መጋቢት 14/2009 . የሙከራ ምርት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ አሁን በምርት ላይ የሚገኙትን ስኳር ፋብሪካዎች (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫአ፣ ከሰምና ተንዳሆ) ቁጥር ወደ ስድስት አድርሶታል፡፡ በተጨማሪ የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ ከጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፉን ስኳር ድርጅት ም/ቤት 53ኛው ጉባኤ በሰኔ ወር ታስተናግዳለች

31895172 1831229803605078 2564437844735033344 nኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፉን ስኳር ድርጅት ም/ቤት 53ኛው ጉባኤ ከሰኔ 18 እስከ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ ማዕከል ታስተናግዳለች፡፡

ጉባዔውን በስኬት ለማስተናገድ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በኩል አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

በጉባኤው ላይ የዓለም አቀፉ የስኳር ድርጅት 87 አባል ሀገራትን ጨምሮ ከ150 - 200 የሚጠጉ የውጪ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የሚገመት ሲሆን፣ በተጨማሪም የስኳር አምራቾች፣ ባለሀብቶች፣ ስኳር ሻጮችና በዘርፉና ተጓዳኝ ምርቶች ዙሪያ ምርምር የሚያደርጉ አካላትም እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ በስኳር ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብትና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ የሀገርና የተቋም ገጽታን ከመገንባት፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግርና ከውጪ ኩባንዎች ጋር በጋራ የማልማት (Joint venture) ዕድል ከማመቻቸት አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፉን ስኳር ድርጅት ም/ቤት 53ኛው ጉባኤ የማስተናገድ ዕድል ያገኘችው ከህዳር 20 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በለንደን በተካሄደው የድርጅቱ 51ኛው የም/ቤት ጉባኤ ላይ ነው፡፡

www.isoethiopia2018.com

በከሰም ስኳር ፋብሪካ የማሻሻያ /ሞዲፊኬሽን/ ሥራዎች ተከናወኑ

በከሰም ስኳር ፋብሪካ በክረምት መደበኛ የጥገና ወቅት ከዲዛይን ችግር ጋር በተያያዘ በኬን ቴብል ላይ በተደጋጋሚ ይከሰት የነበረውን የሸንኮራ አገዳ ብክነት ለመቀነስና ለማስቀረት የሚያስችሉ ውጤታማ የማሻሻያ /ሞዲፊኬሽን/ ሥራዎች መከናወናቸው ተገለፀ፡፡

የፋብሪካው የቴክኒክ ቡድን ሠራተኞች በቡድን መስራት በመቻላቸው ኬንቴብሉን ለመጠገን /በሞዲፊክ/ ለመስራት ይባክን የነበረውን ጊዜ ማስቀረት ከመቻሉ በተጨማሪ ጥራቱን የጠበቀ የማሻሻያ ሥራ በማከናወን ይባክን የነበረውን የሸንኮራ አገዳ መቀነስና ማስቀረት ማስቻሉንም የስራ ክፍሉ ባለሙያ አቶ ሲሳይ ------? ? ? አክለው ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ ባለፈው ዓመት ምንም አይነት አገልግሎት የማይሰጠውን አራት ቁጥር ኬንቴብል በዘንድሮ ምርት ዘመን ወደ አገልግሎት እንዲገባ የማድረግ ስራም ተከናውኗል፡፡

በቴክኒክ ቡድን የተሰሩ እነዚህ የማሻሻያ ስራዎች ፋብሪካው በምርት ዘመኑ ለማምረት ያቀደውን 793.836 ኩንታል ስኳር ያለምንም ብክነት ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው የተገለፀው፡፡

በፋብሪው የቴክኒክ ቡድን ሠራተኞችና ኃላፊዎች ያላሰለሰ ጥረትም የፋብሪካው የምርት ሒደት እንዳይስተጓጎል የሚያስችሉ በርካታ የማሻሻያ ስራዎች ከመከናወናቸው በተጨማሪ በኬን ቴብል ላይ የተከናወነው የማሻሻያ ሥራ የሸንኮራ አገዳ ብክነትን በእጅጉ መቆጣጠር እንደሚያስችል  ተገልጿል፡፡

በሌላ ዜና የከሰም ስኳር ፋብሪካ በትምህርታቸው ብልጫ ውጤት ላስመዘገቡ የሰገንቶ ቀበሌ ት/ቤት ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ በ2009 የትምህርት ዘመን ከአንደኛ  እስከ ስምንተኛ ክፍል አብላጫ ውጤት በማስመዝገብ በደረጃ ላጠናቀቁ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የማበረታቻ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገው ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም ነው፡፡

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተገኑ ገናሞ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት ፋብሪካው ለተማሪዎቹ የሚያደርገው ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች ወደፊት የፋብሪካው ተረካቢዎች መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ አመልክተው ለዚህም በርትተው መማር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን በበኩላቸው የከሰም ስኳር ፋብሪካ ለተማሪዎቹ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም የፋብሪካው ተመሳሳይ ድጋፍ እንደማይለያቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

Top