ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ

Fincha Sugar Factory

የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ አጠቃላይ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የተጀመረው በ1998 ዓ.ም. ነው፡፡ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በአገዳ ልማት በኩል በዌስት ባንክ 8 ሺ 300 ሄክታር በአገዳ የተሸፈነ መሬት እና የኢስት ባንክና ነሼ አካባቢዎችን በማከል ወደ 21 ሺ ሄክታር መሬት ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 7 ሺ ሄክታር በኢስት ባንክ እንዲሁም 4 ሺ 670 ሄክታር በነሼ አካባቢ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የፋብሪካውን አገዳ የመፍጨት አቅም በማሳደግ አመታዊ የስኳር ምርቱን ከ1.1 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል እንዲሁም የኤታኖል ምርትን ከ8 ሚሊዮን ሊትር ወደ 20 ሚሊዮን ሊትር ከፍ ለማድረግ ታቅዶ የማስፋፊያ ሥራው ተካሄደ፡፡

የፋብሪካው ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስራ ተጠናቆ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ማምረት ሂደት ውስጥ የገባ ሲሆን፣ በእርሻ ማስፋፊያ ሥራም ከ19 ሺ ሄክታር መሬት በላይ በአገዳ ለመሸፈን ተችሏል፡፡

በዚህ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በቀን 6 ሺ 600 ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 1 ሚሊዮን 600 ሺ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ነጭ ስኳር የማምረት አቅም ያለው አንድ ተጨማሪ የስኳር ፋብሪካ ተገንብቷል፡፡ ይህ ደግሞ ነባሩ ፋብሪካ ካለው አቅም ጋር ተዳምሮ አጠቃላይ በሁለቱም ፋብሪካዎች የሚመረተውን አመታዊ የስኳር መጠን 2 ሚሊዮን 700 ሺ ኩንታል እንደሚያደርሰው ይጠበቃል፡፡

ለመኖሪያ መንደሮችና ለፋብሪካው አገልግሎት የሚውል የኃይል አቅርቦትን በተመለከተም ፋብሪካው በመሰረታዊነት የራሱን የኃይል ምንጭ ቀደም ሲልም በመጀመሪያው ምዕራፍ ከተተከለ ሁለት ባለ 3.5 ሜጋ ዋት የእንፋሎት ተርባይን ያሟላ ነበር፡፡ በማስፋፊያ የተገነባው ሁለት ባለ 12 ሜጋ ዋት የእንፋሎት ተርባይን ሲጨመርም በድምሩ 31 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይችላል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለፋብሪካው እና ለመስኖ ፓምፖች እንዲሁም ለሠራተኛ መኖሪያ መንደሮች እና ለልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት 21 ሜጋ ዋት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ቀሪውን 10 ሜጋ ዋት ደግሞ ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ማስገባት ተጀምሯል፡፡

Top