መተሐራ ስኳር ፋብሪካ

Methara Factory ethanol

ከወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በመቀጠል በሆላንዱ ኤች ቪ ኤ ተገንብቶ በ1962ዓ.ም ወደ ስራ የገባው የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ፋብሪካው ከ10ሺህ ሄክታር በላይ በሸንኮራ አገዳ የተሸፈነ መሬት ያለው ሲሆን፣ ዓመታዊ አማካይ ስኳር የማምረት አቅሙ በዓመት 136ሺህ 692 ቶን ይደርሳል፡፡

ፋብሪካው ባካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት የኤታኖል ፋብሪካ ገንብቶ ከ2003ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ኤታኖል በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ ኤታኖል የማምረት ዓመታዊ አቅሙም በአመት እስከ 12.5 ሚሊዮን ሊትር ይሆናል፡፡ በተጨማሪ “ባጋስ” ተብሎ ከሚጠራው የሸንኮራ አገዳ ገለባ 9 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የራሱን የኃይል ፍላጎት እያሟላ የሚገኝ እድሜ ጠገብ ፋብሪካ ነው፡፡
ስለ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሲነገር የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍናን ማንሳት የግድ ይላል፡፡ ፋብሪካው ካይዘንን በሚገባ በመተግበርና ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የካይዘን ውድድር በተቋም፣ በልማት ቡድንና በግለሰብ አንደኛ በመሆን የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡

በዚህ ብቻ አላበቃም በተመሳሳይ መስከረም 8 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በተዘጋጀው ሀገር አቀፍ የካይዘን ውድድር ላይ ካይዘንን በማስቀጠል በተቋምና በልማት ቡድን ደረጃ በድጋሚ የአንደኝነት የክብር ሜዳሊያዎችንና ዋንጫዎችን ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ ተቀብሏል፡፡

 

Top