ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ

የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑ በካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አባባ 874 ከ.ሜ ይርቃል፡፡ ፋብሪካው ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ በይፋ የተጀመረው መጋቢት 2/2008 ዓ.ም ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ነው፡፡ ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቀን ከ8,000 አስከ 10,000 ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ እጅግ ዘመናዊ ከመሆኑ አንጻርም የአለም ገበያ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ጥሬ ስኳር (Raw sugar)፣ ነጭስኳር (Plantation white sugar) እና የተጣራ ስኳር (Refined sugar) ማምረት ይችላል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ወደ ሥራ መግባት ስኳር የሚያመርቱትን ፋብሪካዎች ቁጥር ወደ ስምንት (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫአ፣ ከሰም፣ ተንዳሆ፣ አርጆ ዲዴሳ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና 3) አድርሶታል፡፡

የኦሞ ኩራዝ-2 ስኳር ፋብሪካ

DJI 0034 2010110163418

  • በደቡብ ኦሞ ዞን በሰላማጎ ወረዳ የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አባባ 825 ኪ.ሜ ይርቃል፡፡ ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ 6.67 ቢሊዮን ብር ብድር ሐምሌ 2007 ዓ.ም. ግንባታው በይፋ የተጀመረው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ መጋቢት 14/2009 ዓ.ም. የሙከራ ምርቱን ካሳካ በኋላ ወደ መደበኛ ምርት ተሸጋግሯል፡፡

    ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቀን ከ8,000 አስከ 10,000 ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡

ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ

Tendaho Sugar Factoryjpg

በአዋሽ ተፋሰስ ዝቅተኛ አካባቢ በአፋር ክልል በ25 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳን በግብዓትነት የሚጠቀመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ670 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በግዙፍነቱ እና በተሻለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነቱ ጭምር ከሌሎቹ ነባር ስኳር ፋብሪካዎች የሚለየው ይህ ፋብሪካ ከሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ በስተምስራቅ ወደ ጅቡቲ የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ ከጅቡቲ ወደብ በ300 ኪ.ሜ ርቅት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ምቹ ሁኔታም ወደፊት የፋብሪካውን ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

በ1998 ዓ.ም. የፕሮጀክት ሥራው የተጀመረው የግዙፉ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ይዞታ በሚሌ፣ በዱብቲ፣ በአሳኢታ እና በአፋምቦ ወረዳዎች ውስጥ ይገኛል፡፡ OIA (Overseas Infrastructure Alliance) በተባለ የህንድ ኩባንያ የተገነባው ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ከጀመረበት ጥቅምት 2007 ዓ.ም. አንስቶ በመደበኛ የምርት ሂደት ውስጥ ይገኛል፡፡

ፋብሪካው ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ በቀን 13 ሺ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 3 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ስኳር ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ከሚያመነጨው 60 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 38 ሜጋ ዋቱን ለብሔራዊ የኃይል ቋት በማስገባት እንዲሁም 31 ሚሊዮን ሊትር ያህል ኤታኖል በማምረት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን እንደሚያረጋግጥ ይታመናል፡፡

የመጀመሪያው ምእራፍ ፋብሪካ በግብአትነት የሚጠቀመው የሸንኮራ አገዳ ልማት በመከናወን ላይ የሚገኘው በአዋሽ ወንዝ ላይ በተገነባው የተንዳሆ ግድብ አማካይነት ነው፡፡ ከ1.86 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በላይ የመያዝ አቅም ያለው ይህ ግድብ 60 ሺ ሄክታር መሬት እንደሚያለማ ይጠበቃል፡፡

ፋብሪካው በመስኖ የሚለማ መሬት ለአካባቢው አርብቶ አደሮች በማመቻቸቱም አርብቶ አደሩ ወደ ከፊል አርሶ አደርነት መሸጋገር የቻለበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል፡፡

የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

ከ42 ኪ/ሜ በላይ የዋና ቦይና ተያያዥ ስትራክቸሮች ግንባታ ተከናውኗል፤

22,835 ሄ/ር መሬት ውሃ ገብ ተደርጓል፤

የአገዳ ልማት

17,683 ሄክታር መሬት በአገዳ ተሸፍኗል፤

የቤቶች ግንባታ

8,997 የመኖሪያ ቤቶች እና 146 አገልግሎት መስጫ ብሎኮች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፤

የማኀበረሰብ ተጠቃሚነት

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በፕሮጀክቱ፣ በኮንትራክተሮች እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አማካይነት 77,035 ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚ፣ በኮንትራትና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ 84 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም ተደራጅተዋል፡፡

እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ አርብቶ አደሮችን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በዱብቲ 1,667 አባላት ያሏቸውና ህጋዊ ሰውነት ያገኙ 16 የሸንኮራ አገዳ አምራቾች መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ከፋብሪካው ጋር በአውትግሮወር ሞዳሊቲ ትስስር በመፍጠር ሸንኮራ አገዳ በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለህብረተሰቡ ተሳትፎ እና የልማት ሥራዎች በስኳር ኮርፖሬሽን 1.6 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

መተሐራ ስኳር ፋብሪካ

Methara Factory ethanol

ከወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በመቀጠል በሆላንዱ ኤች ቪ ኤ ተገንብቶ በ1962 ዓ.ም. ወደ ስራ የገባው የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ከ10 ሺ ሄክታር በላይ በሸንኮራ አገዳ የተሸፈነ መሬት ያለው ይህ ፋብሪካ በዓመት 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም አለው፡፡

ፋብሪካው ባካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት የኤታኖል ፋብሪካ ገንብቶ ከ2003 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ኤታኖል በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ ኤታኖል የማምረት ዓመታዊ አቅሙም በአመት እስከ 12.5 ሚሊዮን ሊትር ይደርሳል፡፡ በሌላ በኩል "ባጋስ” ተብሎ ከሚጠራው የሸንኮራ አገዳ ገለባ 9 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የራሱን የኃይል ፍላጎት እያሟላ የሚገኝ እድሜ ጠገብ ፋብሪካ ነው፡፡

ስለ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሲነገር የካይዘን ሥራ አመራር ፍልስፍናን ማንሳት የግድ ይላል፡፡ ፋብሪካው ካይዘንን በሚገባ በመተግበርና ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የካይዘን ውድድር በተቋም፣ በልማት ቡድንና በግለሰብ አንደኛ በመሆን የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡

በዚህ ብቻ አላበቃም በተመሳሳይ መስከረም 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በተዘጋጀው ሀገር አቀፍ የካይዘን ውድድር ላይ ካይዘንን በማስቀጠል በተቋምና በልማት ቡድን ደረጃ በድጋሚ የአንደኝነት የክብር ሜዳሊያዎችንና ዋንጫዎችን ከቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ ተቀብሏል፡፡

 

አርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ

የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ፣ በቡኖ በደሌና በጅማ ዞኖች በዲዴሳ ሸለቆ ውስጥ ከአዲስ አበባ ነቀምት በደሌ በሚወስደው መንገድ በ395 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

የአካባቢው ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ በአማካይ 1350 ሜትር ሲሆን፣ የአየር ሁኔታው ሞቃታማ ነው፡፡ አመታዊ አማካይ የዝናብ መጠኑም 1400 ሚሊ ሜትር ይደርሳል፡፡ የዝናብ ሥርጭቱ ደግሞ ከግንቦት እስከ ጥቅምት ይዘልቃል፡፡ በአብዛኛው ጥቁርና አልፎ አልፎ ቀይ ቡናማ አፈር የሚገኝበት ይህ አካባቢ ከአየር ንብረቱ ጋር ተዳምሮ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ምቹና ተስማሚ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

AL-Habasha Sugar Mills PLC ከተባለ የፓኪስታን ኩባንያ በ2005 ዓ.ም. በግዢ ወደ ስኳር ኮርፖሬሽን ይዞታነት የተሸጋገረው ይህ ፋብሪካ በ16 ሺ ሄክታር መሬት የሚለማ የሸንኮራ አገዳን በግብዓትነት በመጠቀም በቀን 8 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱን በተረከበበት ወቅት ሳይጠናቀቅ የቆየ የፋብሪካ ግንባታ ሥራን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ እንዲሁም በወቅቱ ያልነበሩ የልማት ሥራዎችን (የህዝብ አደረጃጀት ሥራ፣ የግድብ ግንባታ፣ የመሬት ዝግጅት፣ የመስኖና የአገዳ ልማት፣ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ እና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች) በማከናወን ፋብሪካውን ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ምርት ማስገባት ተችሏል፡፡

ከስኳር ምርቱ በተጨማሪ ከፍተኛ ኢታኖል የማምረት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ ባጋስ ከተባለ ተረፈ ምርት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ራሱን ከመቻል አልፎ ቀሪውን ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት (ግሪድ) እንደሚያስገባ ይጠበቃል፡፡

አርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተመርቆ ስኳር በማምረት ላይ ይገኛል፡፡

የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

  • ፋብሪካው ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚያውለውን ውሃ ከዲዴሳ ወንዝ ያገኛል፤
  • በኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን አማካይነት ለፋብሪካው ግብዓት የሚውል የሸንኮራ አገዳ ለማልማት በዲዴሳ ወንዝ ላይ ግድብ እየተገነባ ነው፤
  • በተጨማሪ 2 ሺ 300 ሄክታር መሬት የሚያለማ የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ በኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ተካሂዶ 1,600 ሄ/ር መሬት ውሃ ገብ ተደርጓል፤

የአገዳ ልማት

  • 3 ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በአገዳ ተሸፍኗል፤

የቤቶች ግንባታ

  • 124 የመኖሪያ ቤቶችና 11 አገልግሎት መስጫ ብሎኮች ተገንብተዋል፤

የማኅበረሰብ ተጠቃሚነት

  • በምስራቅ ወለጋና በቡኖ በደሌ ዞኖች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ማህበራዊ ተቋማት ተገንብተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶም ለ17,547 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በተለይም የአካባቢው ወጣቶች ልማቱ ባስገኘው የሥራ እድል ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ የመለስተኛ ሙያ ክህሎት ሥልጠናዎች ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር 71 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በአካባቢው ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተዋል፡፡
  • በሌላ በኩል ለአገዳ ማሳ ማስፋፊያ ከአርሶ አደሩ ለተገኘ መሬት የሃብት ንብረትና ምርት ካሳ ክፍያ እንዲሁም ለህብረተሰብ ተሳትፎ እና የልማት ሥራዎች 65.66 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

Top