የስኳር ልማት ንኡስ ዘርፍ ስትራተጂያዊ ማዕቀፍ

የአገራችን ኢኮኖሚ ባለፉት 11 ተከታታይ አመታት በየአመቱ የሁለት አሀዝ ዕድገት የተመዘገበበት ነው፡፡ ይህንን ፈጣን እና መሰረተ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስቀጠል መንግሥት የምዕተ አመቱን የልማት ግቦች ከማሳካት ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 2012-2015 ባሉት አመታት ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ አገራዊ ራዕይ አስቀምጦ ለስኬቱ በጽናት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህ ተልዕኮ ስኬት ባለፉት አመታት የተካሄዱ የልማት ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን፣መልካም ተሞክሮዎችንና የአገሪቱን ራዕይ መሰረት በማድረግ ህዝቡ በየደረጃው በስፋት የተሳተፈበት የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተተግብሮ በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡

በእቅድ ዘመኑ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል አንዱ የገቢ ምርቶችን ለሚተካው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በኢንዱስትሪ ልማት ስትራተጂው መሰረት ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በተለይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ስር የሚመደበው የስኳር ልማት ንኡስ ዘርፍ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

ይህም የሆነው በብዙዎቹ ቆላማ የአገራችን አካባቢዎች ስኳር ለማምረት የሚቻል በመሆኑና በተለይም በእነዚህ አካባቢዎች ለመስኖ ልማት የተመቸና ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት ያለ ከመሆኑ አንጻር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሕዝቡ የኑሮ እድገት ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎት እየጨመረ በመሄዱና የስኳር ምርት ሰፊ የውጭ ገበያ ያለው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የስኳር ልማት ዘርፉን ማስፋፋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የአገራችን ነባር የስኳር ፋብሪካዎች የሚያመርቱት የስኳር ምርት እያደገ የመጣውን የአገር ውስጥ ፍላጎት ማርካት ባለመቻሉ ይህንኑ እጥረት ለመቅረፍ መንግሥት በየአመቱ ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ  በውጭ ምንዛሪ ስኳር ከውጪ አገር አስገብቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ መንግሥት ባለፉት አመታት ባደረገው ርብርብ የወንጂ ሸዋና የፊንጫአ ነባር ስኳር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ፋብሪካዎቹ በከፍተኛ የማምረት አቅም እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ ፋብሪካው ማምረት የጀመረ ሲሆን የአዳዲስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የስኳር ፋብሪካዎቹን በአለም ገበያ በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ ለማድረግ በአውሮፓ ገበያ ለስኳር አምራች የአፍሪካ አገሮች የተሰጠውን ልዩ እድል ለመጠቀም እንዲሁም ከዘርፉ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ነባራዊ ሁኔታዎች እና የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ መሰረት በማድረግ የዘርፉን የልማት እንቅስቃሴ ለመምራትና ለማስፈጸም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 192/2003 ስኳር ኮርፖሬሽን ተቋቁሞ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

 

Top